The first boy diagnosed as autistic
ኦትዝም እንዳለበት የታወቀው የመጀመሪያው ሰው መጨረሻው ምን ሆነ?
(አዘጋጅ፡ መአዛ መንክር፡ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት)
ዶናልድ ግሬ ከህግ ባለሞያ አባቱ እና ከመምህርቷ እናቱ እ.ኤ.አ በ1933 የተወለደ ውብ ልጅ ሲሆን: በተወለደ በ2አመቱ አካባቢም ወላጆቹ ለየት ያሉ ባህሪያትን ማስተዋል ጀመሩ። ባህሪያቶቹም፡
– እናቱ ስሙን ስትጠራውም ሆነ ድምፅ ስታሰማ አለመዞር
– ሁሌም በራሱ አለም መሆን
– ከሰው ይልቅ ከግኡዝ ነገሮች ጋር መጫወትን መምረጥ
– የሰማቸውን ንግግሮች መድገም
– ከእድሜ እኩዬቹ ጋር ለመጫወት አለመፈለግ
– ከሰዎች ጋር የአይን ለአይን ምልከታ አለማድረግ
– እናቱ ወደ ስራ ስትሄድ እንደሌሎች ልጆች ተለየችኝ ብሎ አለማልቀስ
– አንድ ነገር ላይ ለሰአታት አፍጥጦ በማየት መመሰጥ
እና በጣም አስደናቂ እና ከእድሜው በላይ የሆነ ክህሎት ማሳየት (የ2 አመት ልጅ ሆኖ)
– የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 23 በሙሉ በቃሉ ማለት እና የእንግሊዘኛ ፊደሎችን ከሃላ ወደ ፊት ማንበብ መቻልን ነበር።
ይህንን ለየት ያለ ባህሪ ያስተዋሉት ወላጆቹ ወደ ህክምና ተቋም ቢወስዱትም በወቅቱ የልጃቸው ችግር ያልታወቀ እና የአይምሮ ህክምና ክትትል በሚደረግበት ተቋም እንዲኖር ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ ተነግሯቸው በ3 አመቱ ለተቋሙ ሰጥተው ለአንድ አመት በየወሩ እየሄዱ ሲከታተሉት የነበረ ቢሆንም የነበረው ችግር እየባሰ በተለይም የበለጠ ከሰዎች እየተገለለ መምጣቱን ሲያዩ ወደቤታቸው በማምጣት ሊዬ ካነር የተባለ ሳይኪያትሪስት እ.ኤ.አ በ1938 እንዲያየው አደረጉ።
በወቅቱ እንዲህ ለየት ያለ ባህሪ ያሳዩ የነበሩ ሌሎች አስር ህፃናትን ጭምር ረዘም ላለ ግዜ በማጥናት የችግሩ አይነት ኦትዝም የሚባል ስያሜና ከነርቭ እና ባህሪ ጋር ተያያዥነት ያለው እክል መሆኑ ለቤተሰቦቹ ተነገረ።
በወቅቱም የዚህ ችግር ተጠቂ የሆኑ ህፃናት ምን ማድረግ ባህሪያቸውን ሊያሻሽል እንደሚችል ያልታወቀ ቢሆንም የዶናልድ እናት ግን ከሀኪሙ ጋር በመነጋገር ለልጇ ሰፊ ሰአት በመስጠት ይጎሉታል በምትላቸው እራስን የመርዳት ክህሎት፣ ከሰዎች ጋር መቀራረብ ላይ እና ሃሳቡን በንግግር መግለፅ እንዲችል በጣም አድካሚ እና እልህ አስጨራሽ ስልጠና በመስጠት በአስራዎቹ እድሜው ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ በመማር ት/ቱን በሚገባ አጠናቅቆ ኮሌጅ በመግባት በተለይም ከት/ቶች ሁሉ አብልጦ ይወዳችው በነበሩ በሂሳብ እና የፈረንሳይኛ ቋንቋ ጥሩ ውጤት ያመጣ ሲሆን: በፈረንሳይኛ ቋንቋ በዲግሪ ሊመረቅ ችሏል።
ዶናልድ እዚህ ለመድረስ ዋናው ምክንያት፡ የእናቱ ከፍተኛ ድጋፍ እና ስልጠና፣ የእርሱ ትጋት እና ብሩህ አእምሮ እና በአካባቢው እና በትምህርት ቤት የነበሩ ቀና ሰዎች በሙሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
አሁንም አንድን ነገር መደጋገም የሚወድ በተለይም ለቁጥር ካለው ፍቅር የተነሳ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን በስም ከመጥራት ይልቅ በሰጣቸው መለያ ቁጥር የሚጠራ እና ከፍተኛ የሆነ የማስታወስ ችሎታ ያለው ሰው ነው።
ከእድሜ እኩዬቹ ትንሽ ቢዘገይም ስኬታማ ሰዎች ማድረግ የቻሉትን በሙሉ ማድረግ የቻለ፡
-እንደማንኛውም ሰው መኪናውን ያለማንም ድጋፍ በመንዳት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ፣
– ያለድጋፍ ህይወቱን የሚመራ
-ስኬታማ የሆነ የጎልፍ ስፓርት ተጫዋች፣
– ከ40 በላይ ሀገራትን ብቻውን በመጎብኘት የሄደባቸው ቦታዎችን በፎቶግራፍ ማስታወሻ የሚይዝ እና የሂወት ታሪኩ “In A Different Key” በሚል በኦትዝም ታሪክ ላይ በሚያተኩር መፅሃፍ ላይ የሰፈረ የአለማችን ድንቅ ሰው ነው።
ዶናልድ በአሁኑ ሰአት በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ከኦትዝም ጋር የሚኖር የ82 አመት አዛውንት ሲሆን፡ በአካባቢው ባሉ ሰዎች በጣም በስስት የሚታይ፣ የሚወደድ እና በቁልምጫ ዶን ተብሎ የሚጠራ ሰው ነው ።
መጭውን የኦትዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በማስመልከት ይህንን ፅሁፍ Share and like በማድረግ ለሌሌች ያጋሩ።
Source:
Watkins: Forest man first Autism case.
BBC News: Donald Grey Tripplett: The first boy diagnosed as autistic.